Jump to content

ባኃኢ እምነት

ከውክፔዲያ
የባሃይ እምነት አለም አቀፍ ፍርድ ቤት፣ በሃይፋ፣ እስራኤል

ባሃይ እምነት በተለይ በመሥራቹ ባኃኦላህ ጽሑፎችና ትምህርቶች ላይ በ1855 ዓም በፋርስ የተመሠረተ አነስተኛ ሃይማኖት ነው። በዓለም ዙሪያ ከ5 እስከ 7 ሚሊዮን አማኞች ሲኖሩት ባሃዮች በአንዳችም አገር የመንግሥት ሃይማኖት ወይም የሕዝብ ብዛት ከቶ ሆነው አያውቁም። በኢትዮጵያም ቁጥራቸው 27 ሺህ የሆኑት ባሃይ አማኞች ይኖራሉ።

የባሃይ (ፋርስኛ፦ /በሃኢ/ «የክብር») እምነት መነሻ ከሺዓ እስልምና ውስጥ ይቆጠራል። በሺዓ ውስጥ፣ እንዲሁም በፋርስ አገር ያብዛኞቹ ክፍል ውስጥ፣ «የአሥራሁለተኞቹ ወገን» ሲባሉ ይሄ ማለት የነቢዩ መሐመድ 12ኛው ተከታይ ወራሽ ወይም ኢማምሙሃመድ አል-ማህዲ፣ በ5ኛው አመተ እድሜ በ866 ዓም ሳይሞት እንደ ተሰወረ፣ ወደፊትም በመጨረሻ ቀናት ለአለም ፍጻሜው ትግል፣ እርሱ ከኢሳ (ኢየሱስ) ጋር ይታያል የሚል የአብዛኞቹ ሺዓዎች ጽኑ እምነት ነው። ይህም እምነት በእስልምና ትንቢቶች ላይ ይመሠረታል። «የ12ኞቹ ወገን» አማኞች እንግዲህ ከ866 ዓም ጀምረው ለዚሁ ማህዲ ዳግመና እንዲመልስ ጠብቀዋል።

1816 ዓም በፋርስ፣ አህመድ ሻይኽ የተባለ መምህር የሻይኺስምን እንቅስቃሴ መሠረተ፣ ይህም ወገን በተለይ የተነበየ ማህዲን ስለ ማግኘት ልዩ ትኩረት ይሰጥ ነበር። በሻይኽ አህመድ ተከታይ በሲዪድ ካዚም ዕረፍት በ1836 ዓ.ም.፣ የሻይኺስም አማኞች በመላው ፋርስ ማህዲውን ለማግኘት ወጥተው፣ አንድ «ሲዪድ አሊ ሙሐመድ» የተባለ ወጣት አገኝተው «እኔ ለማህዲው መንፈሳዊው በር (ወይም ባብ) ነኝ» አላቸው። ሰውዬውም ከዚያ ጀምሮ «ባብ» በመባል ታውቆዋል፣ እንቅስቃሴውም «ባቢስም» ይባል ጀመር። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ባብ እራሱ የተሠወረው ማህዲ እንደ ነበር ለተከታዮቹ አዋጀ፣ ከዚያም በኋላ ባብ «የአዲሱ ዘመን ነቢይ» በመጨረሻም «የአምላኩ ክስተት» መሆኑን በአዋጆች ገለጸ። ከዚህስ በኋላ የፋርስ ባለሥልጣናት ከቁርዓንሺርክ እንደ ወጣ እንደ ረባሽ ወይም ሀረጤቃ ቆጥረውት አሠሩትና በ1842 ዓም ይሙት በቃ ፈረዱበት።

ባብ «የአዲሱ ዘመን ነቢይ» እየተባለ፣ «የአምላኩ ክስተት ሊመጣ ነው» ስለ ነበየ፣ ከማረፉ ቀጥሎ ቢያንስ ሃያ ሰዎች ደግሞ «እኔ የተነበየው የአምላኩ ክስተት ነኝ» ብለው አሳወቁ። ሚርዛ ሁሰይን አሊ-ኑሪ፣ ወይም ባሃኦላህ ከባቢስም አማኞች አንዱ ሆኖ የፋርስ ባለሥልጣናት ካሠሩት መካከል ነበር። ከእስር ቤት ሲወጣ ከፋርስ በስደት ወደ ኦቶማን መንግሥት ተባረረ፤ በዚያም አገር የባቢስም አማኞች ቅሬታ መሪና የእምነት ጽሑፎች ደራሲ ሆነ። በ1855 ዓም ባሃኦላህ የተነበየው «የአምላኩ ክስተት» እንደ ነበር ያወራ ጀመር፣ ከዚህም በኋላ አዲሱ ሃይማኖት «ባቢስም» ሳይሆን «ባሃይ እምነት» በመባል ይታወቅ ጀመር። ባሃኦላህ ደግሞ «እኔ የአምላኩ ክስተትና የተመለሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ» የሚሉ ደብዳቤዎች ለሮሜ ፓፓ፣ ለንግሥት ቪክቶሪያ፣ እንዲሁም ለፈረንሳይሩስያኦስትሪያ-ሀንጋሪጀርመን ወዘተ. መሪዎች ይልክ ነበር።

አብዱል-ባሃ፣ የመስራቹ የባሃኦላህ ልጅ

ባሃኦላህ በ1884 ዓም ካረፈ በኋላ፣ ልጁ አብዱል-ባሃ የባሃይ እምነት እንቅስቃሴ መሪ እስከ 1914 ዓም ድረስ ሆነ። በ1914 ዓም የአብዱል-ባሃ ልጅ-ልጅ፣ ሾጊ ኤፈንዲ፣ እስከ 1949 ዓም ድረስ መሪነቱን ወረሰው። በነዚህ ዓመት በባሃኦላህ ተወላጆች መካከል ብዙ ክርክሮችና ችግሮች ነበሩ፤ ብዙዎቹም በአብዱል-ባሃ ወይም በሾጊ ኤፌንዲ ቃል ከእንቅስቃሴው ተወገዙ። በ1949 ዓም ሾጊ ኤፈንዲ ያለ ወራሽ ሲያርፍ፣ የባሃይ መሪዎች ከዚያ ወዲያ ማናቸውም አንድያ ላይኛ መሪ እንዳይኖርባቸው ወሰኑ። ከ1955 ዓም ጀምሮ የባሃይ እምነት ላይኛ ሥልጣን በሃይፋእስራኤል የሚገኘው የባሃይ እምነት አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሆኖአል፣ በብዙ አገራት ውስጥ ብዙ በጎ አድራጎት የሚፈጽም ሰላማዊ ሃይማኖት ሆኖአል። የሾጊ ኤፈንዲ መበሊት ሩሒዪህ ኻኑም ከባሃይ እምነት አለቆች አንድዋ ሆና ኢትዮጵያንም በ1961 ዓም በጎበኘችው ጊዜ፣ ንጉሠ ነገሥት በሰላማዊነት ተቀበሉአት።

ሪሂዪህ ኻኑም (ልደት ስም፦ ሜሪ ማክስዌል) የሾጊ ኤፌንዲ ካናዳዊት ሚስት

በባሃይ እምነት ዘንድ፣ የእምነቱ መሥራች ባኃኦላህ እንደ «የአምላኩ ክስተት» እና «የተመለሰው ኢየሱስ» እስካሁን ድረስ ይታያል። «ባብ» ደግሞ በባሃይ እምነት ውስጥ በዮሐንስ መጥምቁና በኤልያስም መንፈስ የመጣ ነቢይ እንደ ነበር ይታመናል።

«የአምላኩ ክስተት» በየሺሁ ዓመታት ያህል ከሰማይ እንደሚላክ ይታመናል፤ ከባኃኦላህ ቀድሞ በታሪክ የተላኩት «የአምላክ ክስተቶች» አዳምኖኅክሪሽናሙሴአብርሃምዞራስተርጎታማ ቡዳ፣ ኢየሱስና ሙሀመድ ይጠቀላሉ። ከባሃኦላህ ዘመን ከአንድ ሺህ አመት በኋላ፣ ወደፊት የሚከተለው «የአምላኩ ክስተት» እንደሚደርስ ይታመናል።

ዕለተ ደይን ወይም የፍርድ ቀን በባሃይ እምነት ዘንድ በዓለም ፍጻሜ የሚደርስ ሳይሆን፣ በየሺሁ አመታት «የአምላኩ ክስተት» በተላከበት ሰዓት በመንፈሳዊነት የሚከሠት ድርጊት ይቆጠራል። እንዲሁም የሙታን ትንሳኤ በባሃይ እምነት ዘንድ የሰውነት ትንሳኤ ሳይሆን መንፈሳዊ ትንሳኤ በተሻለ ዓለም ወይም ህልውና እንደሚሆን ይታመናል።

ማናቸውም ዝሙት ወይም አረቄ መጠጣት በባሃይ እምነት በፍጹም ክልክል ነው፣ ለባሃኦላህ ትምህርቶች ተቃራኒ የሆኑ ሥራዎች ይባላሉ። ከባሃይ እምነት ኢላማዎች መካከል፣ የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድነት፣ በአንድ ሰላማዊነት፣ በአንድ አስተዳደር፣ በአንድ ትምህርት፣ ሃይማኖቶቹንም ሁሉ በአንድ ሃይማኖት በመሲሃቸው በባሃኦላህ ትምህርት ስር ለማዋኸድ ዋናዎቹ ኢላማዎች ናቸው። ከዚህም በላይ የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድ ቋንቋ ለማዋኸድ ይመኛሉ፤ ሆኖም ስለዚሁ ቋንቋ ጸባይ የቱ አይነት ቋንቋ እንደሚሆን ምንም ስምምነት ገና አይኖርም።

  翻译: